የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የሥራ አመራር ማሰልጠኛ ተቋም በ1991 ዓ/ም በአዋጅ ቁጥር 15/1991 ራሱን ችሎ ሲቋቋም ተጠሪነቱ ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እና ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ነበር፡፡ተቋሙ በ1991 ዓ.ም ሲቋቋም የሚከተሉት ተግባር እና ሀላፊነቶች ነበሩት፡–
❖ በክልሉ የሚካሄደውን ስልጠና ስርዓት ባለው መንገድ ለማካሄድና የክልሉን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የስልጠና አሰጣጥን ለማስፈን የሚያስችል ዘዴ ለመቀየስ፣
❖ በክልሉ በየደረጃው ተሰማርቶ የሚገኘውን የሰው ሀይል የስራ አመራር ብቃቱን እንዲያጎለብት አስፈላጊ የሆኑ ስልጠናዎች ለመስጠት የሚሉ አላማዎችን ይዞ ተቋሙ ሀምሌ 27/1991 ዓ.ም በተካሄደው የክልሉ ም/ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ሲቋቋም በአዋጅ ስልጣን ተሰጥቶት በበጀት፣ በሰው ሀይል እና በማቴሪያል ተደራጅቶ በይፋ ስራ የጀመርው ነሀሴ 1/1992 ዓ.ም ሲሆን ያለው የሰው ሀይል ብዛት አንድ ተሾሚ እና 23 ሰራተኞች ነበሩት፡፡ ተቋሙ የራሱ የሆነ ህንጻና ግቢ ከመጀመሪያው ጀምሮ በተቋሙ ደረጃ ለስልጠና ማዕከል ያልተገነባ በመሆኑ ምክንያት ተቋሙ የመቀበል አቅሙ 8ዐ ሰልጣኞችን ብቻ እንዲያስተናግድ
መገደቡ ዋናው ችግር ነበር፡፡ ተቋሙ መስከረም 1995 ዓ.ም በአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ቢሮ ሥር እንዲተዳደር ተደረገ፡፡ ተቋሙ በአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ቢሮ ሥር እንዲተዳደር ሲወሰን በተቋሙና በአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ቢሮ መሀከል መኖር ስለሚገባዉ ግንኙነትና የተቋሙ ተግባርና ኃላፊነትን የመተዳደሪያ መዋቅር የበጀትና ፋይናንስ አጠቃቀም ግልፅ ሆኖ የተቀመጠ አልነበረም፡፡ ተቋሙ መጀመርያ በአዋጅ ሲቋቋም በቦርድ እንደሚተዳደር የተገለፀ ቢሆንም የቦርድ አባላቱ ተዋፅኦና ብዛት በዉል የማይታወቅ በመሆኑ ለተቋሙ መዳከም ተጨማሪ ችግር ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቦርዱ ተቋቁሞ የቦርድ ስልጣን፣ተግባርና ኃላፊነት እንደዚሁም
የተቋሙ ስልጣን፣ ተግባርና ኃላፊነት በተዋረድ በአዋጅ ቢጠቀስም ከላይ እንደተጠቀሰዉ ቦርዱ በአካል ባለመቋቋሙ ተቋሙ የስልጠና፣ የምክር እና ጥናትና ምርምር አገልግሎት በመስጠት ከሚያገኘዉ ገቢ መጠቀም አልቻለም ነበረ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በ1997 ዓ.ም በፊት ሲጠቀምበት የነበረውን ቦታ ለቆ(የአሁኑ የክልሉ ህጻናት እና ሴቶች ጉዳይ ቢሮ የሚገኝበት አጥር ግቢ ውስጥ) አሁን ካለበት አምባ አምስት ለፖሊስ ማሰልጠኛ ከተገነባው ህንጻ ውስጥ እንዲገባ ተደርገ፡፡ ይህም ህንጻ በወቅቱ ለስልጠና ማዕከል ተብሎ ስላልተገነባ ምቹ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የውሀ፣የስልክ መስመር፣የመብራት፣የሻወር እና የሽንት ቤት የኢንስታሌሽን መስመር ዝረጋት ብልሽት ችግሮች ከመኖሩም በላይ ተቋሙን ሥራ ሊያሰራ የሚያስችል ድርጅታዊ መዋቅር ባለመኖሩ ምክንያት ብቃት ያላቸውን አሰልጣኞች እና አማካሪ ባለሙያዎችን መቅጠር ያልቻለበት ሁኔታ ነበር፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ ድጋፍ ሰጪ የሚበዛበት በአንፃሩ ዓላማ አስፈፃሚ ባለሙያ የሚያንስበት ነበር፡፡ በመሆኑም ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች ለመቅረፍ እና የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት መወጣት
እንዲያስችለው ለማድረግ በ2ዐዐ2 ዓ/ም በአዋጅ ቁጥር 89/2ዐዐ2 እንደገና እንዲቋቋም እና እንዲደራጅ ተድርጓል፡፡ በዚህ አዋጅ መሰረት የሚከተሉት ስልጣንና ተግባራት ተሰጥቶታል፡፡
❖ በየደረጃዉ የሚገኙ የክልል የመንግስት አካላት የሥራ አመራር ብቃት እንዲጎለብት አስፈላጊ የሆኑትን፤የሥራ አመራር ስልጠናዎች፤ምርምሮችና የምክር አገልግሎቶች ፍላጎት ያጠናል፤
❖ በጥናትና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ለክልሉ ልማት ኃይሎች ከሥራ አመራር ጋር የተያያዙ የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፤
❖ በተቋሙ የሚሰጡ የሥልጠና፣የምርምርና የምክር አገልግሎቶች ምን ያህል ተጨባጭ ለዉጥ ሊያመጡ እንደቻሉ ለማወቅ የሚያስችል ጥናት በየጊዜዉ ያካሂዳል፤
❖ በሀገሪቱ በተለይም በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት፣ስልጠና ጥናትና ምርምር ተቋማት ጋር በመደጋገፍና በመቀናጀት ይሰራል፤
❖ የስልጠናና የጥናት ፕሮጀክቶች በማዘጋጀት እንዲሁም የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት ከተለያዩ ምንጮች ገቢ የሚያገኝበትን ሁኔታ ይፈጥራል፤ ለሚሰጣቸዉ አገልግሎቶች ተመጣጣኝ ክፍያ ሊያስከፍል ይችላል፣ዝርዝር አፈፃፀሙ በክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ የሚወሰን ሆኖ የሰበሰበዉን ገቢም ለስልጠና፣ለምርምርና ለምክር አገልግሎቶች ማስፋፍያ ይጠቀማል፤
❖ የንብረት ባለቤት ይሆናል፣ዉል ይዋዋላል፣ይከሳል፣ይከሰሳል የሚሉ ስልጣንና ተግባራትን ይዞ የተቋቋም ተቋም ነዉ፡፡
